ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለንግድ ዕድገት
Back

ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለንግድ ዕድገት

Motri
5 min read

ኢትዮጵያ የዲጂታል መሠረተ ልማትን በመጠቀም የንግድ ሥርዓቱን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው።

(አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7 ቀን 2018 ዓ.ም)  ኢትዮጵያ ለኢ-ኮሜርስ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሎጅስቲክስ፣ የክፍያ እና የማርኬቲንግ ሥርዓቶችን በማቀናጀት ንግድን በዲጂታል መሠረተ ልማት አማካኝነት ለማሳደግ በስፋት እየሰራች መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዘርፉ በተጀመረው አዲስ ምዕራፍ፤ የሀገር ውስጥ አምራቾችን በቀጥታ ከሚሊዮኖች ዓለም አቀፍ ሸማቾች ጋር ለማገናኘት እንደ ዲጂታል ኮሪደር ሆኖ የሚያገለግለው ታዋቂዉ የሩሲያ የኦንላይን የገበያ መድረክ "ዋይልድቤሪስ" (Wildberries) በኢትዮጵያ በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡

በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ይድነቃቸው ወርቁ እንደገለጹት፤ የዋይልድቤሪስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በሀገሪቱ የንግድ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

ኢ-ኮሜርስ ጂኦግራፊያዊ መሰናክሎችን በማስወገድ በኢትዮጵያ የተመረቱ (Made in Ethiopia) ምርቶች በቀጥታ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እንዲቀርቡና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲያሳድጉ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያና የሩሲያ የንግድ ልውውጥ ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር እየተጠጋ ቢሆንም የንግድ ሚዛኑ ወደ ሩሲያ ያዘነበለ ነው። በመሆኑም እንደ ዋይልድቤሪስ ያሉ የዲጂታል መድረኮች የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ በማሳደግ ይህንን የንግድ ሚዛን ለማስተካከል ትልቅ ዕድል ይፈጥራሉ።

ዋይልድቤሪስ በሩሲያ፣ በቤላሩስ፣ በካዛክስታንና በሌሎችም ሀገራት ያለውን ሰፊ ተደራሽነት በመጠቀም የኢትዮጵያ ምርቶች አዳዲስ ገበያዎችን እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።

አቶ ይድነቃቸው ለአገር ውስጥ አምራቾችና ላኪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፤ “አሁን የእናንተ ሰዓት ነው” በማለት ዓለም አቀፍ ገበያው በዲጂታል መድረክ አማካኝነት ደጃፋቸው መድረሱን ገልጸዋል። አምራቾች ከዋይልድቤሪስ ጋር በቅርበት በመስራት ስለ ሎጅስቲክስና ዲጂታል ማርኬቲንግ ግንዛቤያቸውን በማሳደግ፤ ምርቶቻቸውን በጥራትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለዓለም ገበያ እንዲያዘጋጁም አሳስበዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለዋይልድቤሪስና ለሌሎች መሰል የቴክኖሎጂ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ፤ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የዜጎች ብልጽግና እንዲረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ሚኒስትር ዴኤታው አረጋግጠዋል።

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6

Tags

#Motri#coffee