ቅንጅታዊ አሠራር ለጥራት ወሳኝ
Back

ቅንጅታዊ አሠራር ለጥራት ወሳኝ

Motri
5 min read

በጥራት ሥራ እምርታዊ ውጤት ለማምጣት ቅንጅታዊ አሠራር ወሳኝ ነው መሆኑ ተገለጸ።

(አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6 ቀን 2018 ዓ.ም) - በኢትዮጵያ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት (የጥራት መንደር) ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ የተጣለባቸውን ተልዕኮ በስኬት ለመወጣት በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ ቅንጅታዊ አሠራር ወሳኝ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥራት መሠረተ ልማትና ማረጋገጫ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ያሉት የዘርፉን የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ከተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ባካሄዱበት ወቅት ነው። በግምገማው ወቅት እንደተመለከተው፤ በዘርፉ የሥራ ክፍሎች እና በአራቱ ተጠሪ ተቋማት የታቀዱ ተግባራት ለሌሎች አርአያ (ሞዴል) ሊሆኑ በሚችል ደረጃ ተፈጽመዋል።

በተለይም በቁጥጥር ሥራ፣ አገልግሎትን በማስፋት፣ ዘመናዊ (Smart) የሥራ አካባቢ በመፍጠር እና ገቢን ከማሳደግ አንፃር ከፍተኛ ሥራ መሠራቱንና አበረታች ውጤት መመዝገቡን አመላክተዋል፡፡

አቶ እንዳለው መኮንን አክለውም “የጥራት መንደር የሀገራችንን ስም እያስጠራ ያለ የመሠረተ ልማት ማዕከል በመሆኑ፣ ባለው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ልክ በተግባርም ውጤታማ ሆኖ መገኘት አለበት" ብለዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያን የጥራት መሠረተ ልማት ከዓለም አቀፍ አሠራሮች ጋር ማስተሳሰር ለተቋማቱ ተልዕኮ መሳካት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አሳስበዋል።

በጥራት መንደር ውስጥ የሚገኙ አራቱ ተቋማት ከዓለም አቀፍ ዕውቅና ጋር የተገናኙ ሥራዎችን የሚሰሩ በመሆናቸው፤ ከዓለም አቀፍ አቻ ተቋማት ጋር በወርክሾፕ፣ በልምድ ልውውጥ እና በቴክኒካዊ ሥልጠናዎች ላይ በመሳተፍ አሠራራቸውን ማዘመንና ማስፋት እንደሚጠበቅባቸው በውይይቱ ላይ ተመልክቷል፡፡

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6

Tags

#Motri#coffee