በበጀት ዓመቱ ባለፋት 7 ወራት ብቻ 5.9 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከወጪ ንግድ ገቢ ተገኝቷል።
አዲስ አበባ: የካቲት 28/2018 ዓ.ም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ በወጪ ንግድ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በዛሬው እለት ውይይት አካሄዷል።
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ያስሚን ውሃብረቢ በበጀት ዓመቱ ባለፉት 7 ወራት ከወጪ ንግድ 5.053 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 5.9 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ገልፀው ይህም የእቅዱን 117% መሆኑንና ከ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ65% ብልጫ እንዳለው አንስተዋል።
ከፍተኛ አፈፃፀም የታየባቸው ማእድን የእቅዱን 148%፣ ከግብርና ምርቶች የእቅዱን 93% ማንፋክቸሪንግ የእቅዱን 86.1% መሆናቸውን ተገልጿል።
ለእቅድ አፈፃፀሙ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ሀገራችን በወሰደችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣት፣ የገበያ መዳረሻዎችን የማሳደግ ስራ መሰራቱ፣ በህገወጥ የምርት ክምችት ላይ እየተደረገ ባለው ክትትልና ቁጥጥር ምክንያት ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች መጠን መጨመርና የማነፃፀሪያ ዋጋ ተመን የአለም አቀፍ የዋጋ ተለዋዋጭነትን እየተከተለ በየወቅቱ ክለሳ መደረጉ እንደሆነ ወ/ሮ ያስሚን ገልፀዋል።






