ለህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ተቋማት በሙሉ!!
የጋዜጣዊ መግለጫ መሪ ርዕስ፡ የዓለም የቡና ገበያ መቀዝቀዝን ታሳቢ ያደረገ አስቸኳይ ጥሪ
አዲስ አበባ
የካቲት 26/2018
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ፣ ዛሬ ከተለያዩ የመንግስት እና የግል ሚዲያ ተቋማት ለተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በወቅታዊ የቡና ገበያ ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫውም የዓለም የቡና ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ተከትሎ፣ የዘርፉ ተዋናዮች ሊደርስባቸው ከሚችል ከፍተኛ ኪሳራ ራሳቸውን እንዲከላከሉ አሳስበዋል።
1. ወቅታዊው የዓለም የቡና ገበያ ሁኔታ
ባለፉት ጥቂት ወራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና መሸጫ ዋጋ ከፍተኛ መውረድ እያሳየ ይገኛል። ይህንን ሁኔታ አስቀድሞ በመተንበይ፣ የግብርና ሚኒስቴር እና የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከቡና ተዋናዮች ጋር በተደጋጋሚ ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
በተለይም ባለፈው ሳምንት መግቢያ ላይ በተካሄደው መጠነ-ሰፊ መድረክ፣ በሳይንሳዊ ትንታኔ የተደገፈ መረጃ የቀረበ ሲሆን፣ የገበያው አዝማሚያ አሳሳቢ መሆኑና ተዋናዮች በእጃቸው ያለውን ምርት በፍጥነት ወደ ገበያ ካላቀረቡ ለከፋ ኪሳራ ሊዳረጉ እንደሚችሉ መግባባት ላይ ተደርሷል።
2. የምርት ግዢና የዋጋ ስጋት
ምርት ከመሰብሰቡ በፊት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ባደረገው ጥናትና የቅድመ-ማስጠንቀቂያ መረጃ መሠረት፣ ምርት በተጋነነ ዋጋ መግዛት እንደማይገባ ማሳሰቢያ የሰጠ ቢሆንም በርካታ አርሶ አደሮች፣ አቅራቢዎች እና ላኪዎች "እንደ አምናው በከፍተኛ ዋጋ ይሸጣል" በሚል የተሳሳተ ግምት፣ በውድ ዋጋ መግዛታቸውን እና ማከማቸታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ነገር ግን ቡና የአገር ሀብት በመሆኑ ያለ አግባብ ማከማቸት ከፍተኛ ተጠያቂነትን ከማስከተሉ በዘለለ፣ ምርቱን ይዞ መቆየት የኪሳራውን መጠን ይበልጥ ያሰፋዋል።
3. የተላለፈ አስቸኳይ ጥሪ
ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ በመግለጫቸው ማጠቃለያ ላይ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፦
• ፈጣን የገበያ ተሳትፎ፡ ተከማችቶ የሚገኝ ቡና በወቅታዊው የዓለም ገበያ ዋጋ ሳይሸጥ መቆየቱ ኪሳራን ከማባባስ ባለፈ ለሀገር የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬም ይጎዳል። ስለዚህ ተዋናዮች ምርታቸውን ሳይዘገዩ ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ።
• የገበያ መረጃን መከታተል፡ የዘርፉ ተዋናዮች ግዢ ሲፈጽሙም ሆነ ምርት ሲያቀርቡ ስሜታዊነትን በማስወገድ፣ በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚወጡ ሳይንሳዊ የገበያ ትንታኔዎችንና መረጃዎችን መሠረት እንዲያደርጉ፣ ከዚህ በተጨማሪ ለአንድ ዓመት ያህል የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ በዚሁ ሊቀጥል እንደሚችል ተገንዝበው በእጃቸው ያለውን ቡና በአፋጣኝ ለገበያ እንዲያቀርቡም አሳስበዋል።
• ክቡር ዶ/ር አዱኛ ሀገራዊ ሀህገወጥነትን ለመከላከል እንዲቻል የኮንትሮባንድ ግብረኃይል መቋቋሙን ጠቁመው፤ በኮንትሮባንድ ለመላክ ጥረት የሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርግም አብራርተዋል።
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከመንግስት ጋር በመተባበር የቡና ተዋናዮች ጥቅማቸው እንዲጠበቅና የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነት እንዲቀጥል አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።
