የቻይና ቡና በአውሮፓ ገበያ
Back

የቻይና ቡና በአውሮፓ ገበያ

ECTA
5 min read

ቻይና በአውሮፓ ገበያ የቡናውን ዘርፍ በዝቅተኛ ዋጋ እና በከፍተኛ ቅልጥፍና እየተቀላቀለች ነው!!

• አውሮፓ ከአለም አቀፍ የቡና ፍጆታ ከ32% በላይ የሚሆነውን ድርሻ በመያዝ ለገበያ ምቹ የሆነች ቀጠና ናት።

• የቻይና የንግድ ምልክቶች የቡና አጠቃቀም ባህልን እስከ ምን ድረስ ሊቀይሩት እንደሚችሉ ገደብ ቢኖርም፣ ገበያውን ግን ወደ ተለያዩ ዘርፎች (Segmentation) እንደሚከፍሉት ይጠበቃል። .........

ቻይና በአውሮፓ ገበያ የቡናውን ዘርፍ በዝቅተኛ ዋጋ እና በከፍተኛ ቅልጥፍና እየተቀላቀለች ነው!!

• አውሮፓ ከአለም አቀፍ የቡና ፍጆታ ከ32% በላይ የሚሆነውን ድርሻ በመያዝ ለገበያ ምቹ የሆነች ቀጠና ናት።

• የቻይና የንግድ ምልክቶች የቡና አጠቃቀም ባህልን እስከ ምን ድረስ ሊቀይሩት እንደሚችሉ ገደብ ቢኖርም፣ ገበያውን ግን ወደ ተለያዩ ዘርፎች (Segmentation) እንደሚከፍሉት ይጠበቃል።

ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ፣ የቡና ችርቻሮ ንግድ በታወቁ አሰራሮች አማካኝነት ዓለም አቀፋዊ ሆኗል፤ ይህም "ቡና ቤት" ምቾትንና ድባብን (Atmosphere) ከአገልግሎት ቅልጥፍና ጋር አቀናጅቶ የያዘ "ሦስተኛው ስፍራ" (Third place) ተብሎ ይጠራ ነበር። አሁን ግን አዲስ ሞዴል ብቅ ብሏል፤ ይህ ሞዴል በልምድ ወይም በድባብ ላይ ሳይሆን በፍጥነት፣ በስፋት እና በዝቅተኛ ዋጋ ላይ የተገነባ ነው።

የቻይና የቡና ብራንዶች በፍጥነት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እየገቡ ነው። ይዘውት የመጡት የሥራ ሥርዓትም በሞባይል መተግበሪያ (App) ትዕዛዝን መቀበል፣ ጥቅጥቅ ያሉ የመሸጫ ቅርንጫፎች እና አስገራሚ የዋጋ ቅናሽ ላይ ያተኮረ ነው። እነዚህ ተቋማት የቡናን ባህል ሳይሆን፣ የአሰራር ቅልጥፍናን ወደ ውጭ እየላኩ (Export እያደረጉ) ነው።

አውሮፓ በከፍተኛ የቡና ፍጆታዋና እየጨመረ በመጣው ዋጋ ምክንያት ቀጣዩ ተመራጭ መዳረሻቸው ሆኗል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ፣ ዝቅተኛ ዋጋና ከፍተኛ ቅልጥፍና ያላቸው ኦፕሬተሮች ወደ ገበያው ከመግባት ባለፈ፣ የገበያ ድርሻን ለመቆጣጠርና ቡና በከፍተኛ ደረጃ የሚሸጥበትን መንገድ ለመቀየር አመቺ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

የተለየ ዓይነት ፉክክር

የቻይና የቡና ሰንሰለቶች መስፋፋት ከአዳዲስ የገበያ ተወዳዳሪዎች መምጣት በላይ ትርጉም አለው። ይህ በአውሮፓ የቡና ችርቻሮ ንግድ ውስጥ መሰረታዊ የሆነ የተለየ አቀራረብን ያስተዋውቃል።

ከቻይና ግዙፍ የቡና ብራንዶች አንዱ የሆነው ኮቲ ኮፊ (Cotti Coffee)፣ በ28 አገራት ውስጥ ከ10,000 በላይ መሸጫዎች አሉት። እ.ኤ.አ. በ2026 መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ስፔን ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ ጣሊያን፣ ቤልጂየም፣ ፖርቱጋል እና ኔዘርላንድስ ለመስፋፋት ማቀዱ ተገልጿል።

ምንም እንኳን በአካል በአውሮፓ ገበያ ገና ባይታይም፣ ሉኪን ኮፊ (Luckin Coffee) ከ30,000 በላይ ሱቆችና 450 ሚሊዮን ደንበኞች ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ በእስያና በአሜሪካ መስፋፋቱን ቀጥሏል። ወደ አውሮፓ ገበያ ለማምራት ባለው እቅድ ውስጥ የአውሮፓ ትልቁን የቡና ሰንሰለት የሆነውን ኮስታ ኮፊን (Costa Coffee) የመግዛት ፍላጎት እንዳለውም ተዘግቧል።

የ"ኮፊ ኮንሱሌት" (Coffee Consulate) መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ስቴፈን ሽዋርዝ እንዲህ ይላሉ፡-

“ይህ እጅግ ትልቅ ለውጥ ነው፤ ምክንያቱም ወደ ውጭ እየተላከ ያለው ብራንድ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ‘የአሰራር አመክንዮ’ (Operating logic) ነው። ይህ ከአሁን በኋላ የቻይና የሀገር ውስጥ የንግድ ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ በአለም አቀፍ የቡና ችርቻሮ ዘርፍ አዲስ የፉክክር ሞዴል መከሰቱን የሚያሳይ ነው።”

ይህ "የአሰራር ሞዴል" ከልምድ ይልቅ ለውጤት (Output) ቅድሚያ ይሰጣል። አነስተኛ የመሸጫ ስፍራዎች፣ በመተግበሪያ የሚመራ ትዕዛዝ እና ፈጣን ርክክብ ባህላዊውን የቡና ቤት ድባብ ይተካሉ። ዋጋውም በተመሳሳይ ገበያውን የሚረብሽ ነው፤ ለምሳሌ በጀርመን የሚገኘው ኮቲ ኮፊ የአንድ ኤስፕሬሶ ዋጋ €0.99 እና የካፑቺኖ ዋጋ ከ**€3** በታች እንዲሆን አድርጓል፤ ይህም ከአካባቢው ነባር ዋጋዎች እጅግ ያነሰ ነው።

አውሮፓ ለምን ተመረጠች? እድሉስ የት ጋር ነው?

ይህ አዲስ ሞዴል፣ የቡና ጥራትን ደንበኛው በቦታው ቆይቶ ከሚያሳልፈው ምቹ ጊዜ ጋር አጣምሮ ከቆየው ከአውሮፓ የቡና ገበያ ጋር በእጅጉ ይቃረናል።

ውጤቱም ነባሩን ሞዴል በቀጥታ መተካት ሳይሆን፣ ጎን ለጎን በማራመድ ነው። የቻይና የቡና እሴት ሰንሰለቶች የአውሮፓን የቡና ባህል ለመድገም እየሞከሩ አይደለም፤ እነሱ እየተወዳደሩ ያሉት ሙሉ በሙሉ በሌላ መስክ ነው።

ወቅቱ ለዚህ ሽግግር ወሳኝ ነው። የአውሮፓ የቡና ገበያ በጥሬ ቡና ዋጋ መናር፣ በጉልበት (Labor)፣ በቤት ኪራይና በኢነርጂ ወጪ መጨመር ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ነው።

አውሮፓ እ.ኤ.አ በ2025 የዓለምን 32% ፍጆታ በመሸፈንና በነፍስ ወከፍ ከፍተኛ የቡና ተጠቃሚ አገራትን በመያዝ ቀዳሚነቷን ቀጥላለች። ይህ ከፍተኛ ፍጆታና እየጨመረ የመጣው ዋጋ ዝቅተኛ ወጪ ለሚጠይቁት ተዋናዮች ግልጽ የሆነ የመግቢያ በር ከፍቷል። ቢሆንም ግን፣ ዶ/ር ስቴፈን ርካሽ አማራጮች ቢመጡም ደንበኞች ጥራት ያለውን (Specialty) ቡና ግን በፍጹም እንደማይተዉ ያምናሉ።

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የዋጋ መጨመር ደንበኞች በልዩ ሁኔታ የሚዘጋጅ ቡናን እንዲተዉ አያደርጋቸውም። ይልቁንም፣ የዋጋ ጫናው በሁለት የተለያየ የፍጆታ አይነቶች መካከል ያለውን ልዩነት ያሰፋዋል፡-

1. ቡና እንደ ልምድ (Coffee-as-experience): ለጣዕም፣ ለባህልና ለጥራት የሚጠጣ።

2. ቡና እንደ የዕለት ተዕለት ልማድ (Coffee-as-functional habit): ለስራ ወይም ለመንገድ በፈጣንና በዝቅተኛ ዋጋ የሚፈለግ።

“ያ የፍጆታ ክፍተት ነው እጅግ ቀልጣፋ ተወዳዳሪዎች ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉበት ቦታ፣” ሲሉ ስቴፈን ያጠቃልላሉ።

ይህ የገበያ ፉክክር የዘርፉን የገበያ ዑደት ይቀይረው ይሆን?

ሳህለማርያም ገ/መድህን

ምንጭ ያደረኩት Coffee Intellegence ነው:

https://intelligence.coffee/.../chinese-coffee-brands.../...

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2

Tags

#ECTA#coffee