የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት ተደራዳሪ ልዑክ ከዩናይትድ ኪንግደም ቋሚ ተወካይ ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሄደ።
ሚያዝያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም (ጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ)፦በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ዋና የንግድ ተደራዳሪ ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባልነት ልዑካን ቡድን፤ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በዓለም ንግድ ድርጅት የዩናይትድ ኪንግደም ቋሚ ተወካይ ከሆኑት አምባሳደር ኩማር አየር ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂዷል።
ክቡር ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ዩናይትድ ኪንግደም በድርጅቱ የአባልነት ሂደት ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ድጋፍና በተለይም 7ኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ በስኬት እንዲጠናቀቅ በሊቀመንበርነት ለተጫወተችው ገንቢ ሚና ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም በመከባበር ላይ የተመሠረተና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ሁለንተናዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን የንግድ ሥርዓትን መቀላቀል ይህንን ነባርና ጠንካራ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንዲሁም ሰፊ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመክፈት አቅም እንደሚፈጥር በውይይቱ ተነስቷል።
አምባሳደር ኩማር አየር በበኩላቸው፤ ዩናይትድ ኪንግደም የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድሩን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እና የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ስኬታማ እንዲሆን ያላትን ጽኑ አቋምና ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።




