የጅጅጋ ፎረም ተጀመረ
Back

የጅጅጋ ፎረም ተጀመረ

Motri
5 min read

የጅጅጋ ፎረም ተጀመረ፤ “በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ቀጣናዊ አጋርነትን ማጠናከር” በሚል መሪ ቃል ውይይት እየተደረገ ነው።

(ጅጅጋ፤ ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም) — በሶማሌ ክልል መንግሥት፣ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና ለኃላፊነት የተሞላበትና ሰላማዊ ፖለቲካ ማዕከል (Centre for Responsible & Peaceful Politics) በጋራ የተዘጋጀው “የአፍሪካ ቀንድ የምሁራን የጋራ ውይይት” (Horn Inter-Elite Dialogue / Jigjiga Forum) በጅጅጋ ከተማ በይፋ ተጀምሯል ።

በፎረሙ መክፈቻ ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ሙስጠፋ መሐመድ ኡመር፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ስትራቴጂካዊ አጋሮች ተገኝተዋል ።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) መድረኩ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባሉ የሰላም፣ የደኅንነት፣ የሥራ አመራር፣ የትብብር እና የቀጣናዊ መረጋጋት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመምከር የተዘጋጀ ወቅታዊና ወሳኝ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል ።

የቀጣናው ውስብስብ ፈተናዎችና የትብብር አስፈላጊነትን በተመለከተ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በጂኦፖለቲካዊ ፉክክር፣ በስትራቴጂካዊ የአሰላለፍ ለውጦች እና የሀገራትን የሉዓላዊነትና የልማት ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ጉዳዮች የመወሰን ነፃነት በሚፈታተኑ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፈ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ከዚህ በተጨማሪም እንደ የድንበር ተሻጋሪ ግጭቶች መስፋፋት፣ አክራሪነት፣ ሕገ-ወጥ ንግድና የገንዘብ ዝውውር ያሉ ችግሮች በቀጣናው ሰላምና የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑን አስረድተዋል ።

እነዚህን ችግሮች በተናጠል መፍታት እንደማይቻልና እንደ ጅጅጋ ፎረም ያሉ አካታች የምክክር መድረኮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣትና የጋራ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስርን ለማጠናከር ወሳኝ መሠረት መሆናቸውን አብራርተዋል ።

የኢትዮጵያ “ሀገር በቀል” መፍትሔዎች እና የ“መደመር” ፍልስፍና ኢትዮጵያ እያጋጠሟት ያሉትን የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የምጣኔ ሀብት ፈተናዎች በሀገር በቀል ዕውቀት፣ በባለቤትነት ስሜትና በአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ በተመሠረቱ መፍትሔዎች ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኗን ሚኒስትሩ ገልጸዋል ።

ለዚህም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የቀረበው የ“መደመር” ፍልስፍና ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ፤ መደመር ማለት “ልዩነትን ጠብቆ በኅብረት ለዕድገት መቆም” በመሆኑ፣ ይህ አስተሳሰብ ድንበር የተሻገረ ቀጣናዊ ትብብርንና ሰላምን ለማስፈን ትልቅ አቅም እንደሚሆን አስገንዝበዋል ።

የምጣኔ ሀብት ሪፎርም እና የቀጣናዊ ትስስር ጥረቶችን በተመለከተም ክቡር ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው ያለው ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ አጀንዳ (HGER) የግል ዘርፉን በማበረታታት የማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር የታለመ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ሪፎርሙም ሀገሪቱን ለቀጣናዊ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ዝግጁ እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል ። ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር እየሠራች መሆኑን አብራርተዋል ፦ በመሠረተ ልማት ትስስር በተለይም የሎጅስቲክስ ሥርዓትን ማዘመን፣ የመኪናና የባቡር መስመሮችን ማስፋፋት፣ የደኅንነቱ የተጠበቀ የወደብ አገልግሎት አጠቃቀምን ማሳደግ እና የትራንስፖርት ኮሪደሮችን ከጎረቤቶች ጋር ማገናኘት እንዲሁም ኃይል ኤክስፖርትን በተመለከተ ደግሞ ለጎረቤት ሀገራት ንጹህና ተመጣጣኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የቀጣናውን የምጣኔ ሀብት ዕድገት መደገፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ አስታውቀዋል ።

የንግድ ፖሊሲና ሥርዓት ማሻሻያን በተመለከተም የታሪፍና ከታሪፍ ውጪ የሆኑ የንግድ ማነቆዎችን መቀነስ፣ የአሠራር ደረጃዎችን ማጣጣም እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ስምምነትን ተግባራዊ ማድረግ ዋነኛው መሆኑን ጠቁመዋል ።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም ሲሰፍን ሁሉም ሀገራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በጽኑ እንደምታምን የገለጹት ሚኒስትሩ ፤ በመሠረተ ልማት፣ በኃይል ትስስርና በንግድ ማመቻቸት ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች የምጣኔ ሀብት ዕድልን፣ የፖለቲካ መረጋጋትንና ማኅበራዊ ትስስርን በጋራ የሚያሳድጉ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ መተማመን ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ቀጣና ለመገንባት መሥራቷን ትቀጥላለች ብለዋል ።

በመድረኩ ላይ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች፣ የሰላም ሚኒስትር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም እንዲሁም የኢጋድ ሊቀመንበር እና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ታድመዋል ።

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6
Gallery image 7
Gallery image 8
Gallery image 9
Gallery image 10

Tags

#Motri#coffee