የልዩ ጣዕም ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል
ዲላ ፤ታህሳስ 25/2018
በበጀት ዓመቱ የልዩ ጣዕም ቡናን በብዛትና በጥራት አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የዘርፉን ገቢና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ የልዩ ጣዕም ቡና ዝግጅት የመስክ ምልከታና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተለያዩ ጣዕም ቡና ማቀነባበሪያ ማሽን ስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት በተያዘው ዓመት ቡናን በብዛትና በጥራት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ርብርብ እየተደረገ ነው።
በተለይ በቂ ምርት ከማዘጋጀት ባለፈ ጥራትና እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ ጣዕሞች ቡናን የሚያቀነባበር ማሽን ወደ ስራ መግባቱን ለአብነት አንስተዋል።
ይህም የኢትዮጵያን ቡና ተፈላጊነት ለመጨመር የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
በተያዘው ዓመት ከ600 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በጥራት የመሰብስብና የማዘጋጀት እንዲሁም ከስር ከስር የመላክ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በተለይ የውጭ ደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የልዩ ጣዕም ቡና ከ70 በመቶ በላይ በማቅረብ ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘትና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በክልሉ ከ131 ሺህ ቶን በላይ ቡና በመሰብሰብ ከ46 ሺህ ቶን የሚልቀውን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አማኑኤል ብሩ ናቸው።
በተለይ ከታጠበና ካልታጠበ ቡና በተጨማሪ የቡና ገዢ ደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ቡና በተለያዩ ጣዕሞች በስፋት እየተዘጋጀ መሆኑን አንስተው ምልከታውም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ብቻ ልዩ ጣዕምን ጨምሮ በ15 የተለያዩ ጣዕሞች ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ቡና ለውጭ ገበያ መቅረቡን አንስተው ይህም የዞኑን ቡና ጥራትና ተፈላጊነት በእጅጉ ማሳደጉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በማህበራትና በአርሶ አደሮች የቡና ግዢ ደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የልዩ ጣዕም ቡና በስፋት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ከአካባቢው ማህበራት ጋር በመቀናጀት በውድድር የሚሸጥ ልዩ ጣዕም ቡና እያዘጋጁ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የቡና ላኪ ድርጅት ስራ አስኪያጅ የሆኑት መሰረት ወርቅነህ ናቸው።
በዚህም በተያዘው ዓመት 5 ሺህ ቶን ልዩ ጣዕም ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብም ቡናን በተለያዩ ጣዕሞች የሚያዘጋጅ ማሽን ወደ ስራ ማስገባታቸውን ገልጸዋል።
መረጃውን ያገኘነው ከኢዜአ ነው
