የተቀላቀሉ እና ጣዕም የተጨመረባቸው ቡናዎች
Back

የተቀላቀሉ እና ጣዕም የተጨመረባቸው ቡናዎች

ECTA
5 min read

የተቀላቀሉ (Co-fermented) እና ጣዕም የተጨመረባቸው (Infused) ቡናዎች የደንበኞችን ፍላጎት እየቀየሩ ይሆን?

ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደ ብርቱካን፣ እንጆሪ፣ ቸኮሌት፣ ቅመም ወይም የአበባ መዓዛ ያሉ የጣዕም መገለጫዎች (Tasting notes) አብዛኛውን የልዩ ቡና ተጠቃሚ ለማርካት በቂ ነበሩ። ዛሬስ?

ዛሬ ዛሬ ደግሞ ተጠቃሚዎች እንደ ዶናት፣ ከረሜላ፣ ትሮፒካል ፐንች፣ የእርጎ እና ፒች ሻይ የሚሉ ስያሜዎች የተለጠፉባቸውን ቡናዎች እየጠጡ ይገኛሉ። ብዙዎቹ ተጠቃሚዎችም እንደዚህ "ጠንከር ያሉ" እና ገንነው የሚወጡ የቡና ጣዕሞችን የመፈለግ አዝማሚያ ላይ እንዳሉ አንዳንድ በዘርፉ የተከተቡ ጽሁፎች ያመላክታሉ፡፡

ለዚህ ነው ጣዕም የተጨመረባቸው (Infused) እና ከሌሎች ፍራፍሬዎች ጋር አብረው እንዲብላሉ የተደረጉ (Co-fermented) ቡናዎች በአሁኑ ወቅት በልዩ ቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ አወዛጋቢ አጀንዳዎች እየሆኑ የመጡት።

እነዚህ ቡናዎች ለምን በፍጥነት እየተስፋፉ መጡ?

ምክንያቱም እነዚህ ቡናዎች፦

• ለመረዳት ቀላል ናቸው

• ለገበያ ለማቅረብ ይመቻሉ

• በአእምሮ ውስጥ በቀላሉ ይታወሳሉ

ለአዳዲስ ተጠቃሚዎች፣ ንጹህና በባህላዊ መንገድ ታጥቦ የተዘጋጀ ቡና ጣዕሙ "ረቂቅ" ወይም ግራ የሚያጋባ ሊሆንባቸው ይችላል። ነገር ግን በአናይሮቢክ ዘዴ የፍራፍሬ ጣዕም ያለው ቡናስ? ይህንንም በተመለከተ የዘርፉ ሰዎች እንደሚሉት ተጽዕኖው ፈጣን ነው፣ ምላሹ ቅጽበታዊ ነው፣ የቀመሳ (Cupping) ልምድም አይጠይቅም፡፡ በመሆኑም ይህ ሁኔታ ደንበኞች "ጥሩ ቡና" የሚለውን ትርጉም የሚረዱበትን መንገድ እየቀየረው ነው።

ትልቁ ለውጥ፦

ዛሬ የቡናው ጣዕም ከቡናው መገኛ Origin/ "ይህ ቡና ከየትኛው አካባቢ የመጣ ነው?" ከሚለው የደንበኞች ፍላጎት ባሻገር "ጣዕሙ ምን ይመስላል?" የሚለው ጉዳይ መሰረታዊ ጥያቄ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን የባለልዩ ጣዕሞች ቡና የንግድ ግንኙነት ወዴት ሊሄድ ይችል ይሆን የሚለውን ጉዳይ ከወዲሁ ለመገመት የሚያዳግት አይመስልም።

ይህ ማለት ግን ባህላዊ /Washed, unwashed ቡናዎች ችግር ይገጥማቸው ይሆናል ደግሞ ማለት አይደለም::

እንዲያውም ብዙ ልምድ ያላቸው የቡና ጠጪዎች ቀስ በቀስ ወደሚከተሉት እየተመለሱ ነው፦

• ወደ ንጹህ ጣዕም (Cleaner cups)

• ግልጽ ወደሆነ አዘገጃጀት (Transparent processing)

• የአካባቢን ለምነትና መዓዛ ወደሚያሳዩ ቡናዎች (Terroir-driven)

• ከከባድ ጣዕም ይልቅ ለጥራትና ለንጽህና ቅድሚያ መስጠት

እውነታው፦

ከፍራፍሬ ጋር አብረው የቦኩ (Co-fermented) ቡናዎች ልዩ ቡናን እየተኩት አይደለም፤ ይልቁንም የገበያውን አማራጭ እያሰፉት እንጂ።

የልዩ ቡና የወደፊት ዕጣ ፈንታ በባህላዊ መንገድ የታጠቡ ቡናዎች ወይም በጣም ኃይለኛ ጣዕም ያላቸው የተቀላቀሉ ቡናዎች መካከል ባለ የገበያ ጨዋታ ሜዳ መካከል ይመስላል፡፡ ይልቁንም የወደፊቱ ጊዜ የሚሆነው በሁለቱም መሃል ያለውን ሚዛን ለሚረዱ አምራቾችና ቆዪዎች ነው።

ለእርስዎ እንደ አንድ የዘርፉ ባለሙያ፤ እነዚህ Co-fermented እና ጣዕም የተጨመረባቸው (Infused) ቡናዎች የኢትዮጵያን ባለ ተፈጥሯዊ መዓዛ (Original Terroir) ሊፎካከሩ ይችላሉ ወይስ አዲስ የገበያ ዕድል ይፈጥራሉ?

ለእኔ ተፈጥሯዊ፣ ኦርጋኒክ፣ በርካታ ጣፋጭ፣ ውስብስብ እና ለዛ ያለውን የኢትዮጵያ ቡና ሊፎካከር አይደለም ጫፉ ሊደርስ አይችልም እላለሁ፡፡ ነገር ግን በጣም በጥራት እስከተዘጋጀ እና ባለልዩ ጣዕም የሚለውን መስፈርት እስካሟላ ድረስ፡፡

እናንተስ? እስኪ አስተያየት ስጡበት፡፡

በሳህለማርያም

Gallery

Gallery image 1

Tags

#ECTA#coffee